የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን በመከላከል ሂደት የአሰሪና ሰራተኛ ወገኖች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
🇪🇹ታህሳስ 2/2018 ዓ.ም🇪🇹
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ዓለም አቀፍ
የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ <<ተግዳሮቶችን በመቋቋም ፤ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምላሽን እናረጋግጣለን>> በሚል መሪ ሐሳብ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ መክፈቻ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ተቀባ ባሰሙት ንግግር ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭትን ለማቆም ስምምነት ከፈረሙ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኑን በመግለፅ በዚህም የስራ ቦታ የኤችአይቪ ኤድስ መከላከል ፓሊሲ ቀርፃ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የመስጠት ተግባር በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭትን ማቆም ለሌሎች ስራዎች መነቃቃትን ይፈጥራል ያሉት ኃላፊው በሽታውን በመከላከል ሂደት የአሰሪና ሰራተኛ ወገኖች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የአሰሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተወካይ የሆኑት አቶ መስፈን ለገሰ በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን በስራ ቦታ ላይ መከላከል አትራፊ መሆኑን በመገንዘብ የህብረተሰቡ አካል የሆነውን ሰራተኛ ከቫይረሱ ለመጠበቅ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ቫይረሱ ያለ ሰራተኞች ተሳትፎ አይቀንስም ያሉት የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ተወካይ አቶ ዘሪሁን ገዛኸኝ ምርትና ምርታማነትን እንዳይቀንስ በማድረግ ሂደት በፓሊሲ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ወደ ተግባር ላይ በማዋል አሁን ላይ የሚስተዋለውን መዘናጋት ለመቀልበስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በፓናል ውይይቱ ቀኑን የተመለከቱ የተለያዩ ሰነዶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትውልድህን አድን ፀረ ኤድስ ኮሚቴ የስራ እንቅስቃሴ ተሞክሮ ቀርቧል።
በዕለቱም ቀኑን በተለያዩ ሁነቶች በማክበር ተሳትፎ ላደረጉ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።
በዓለም ላይ ቫይረሱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1981 ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 32.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዓለም አቀፉ የፀረ ኤችአይቪ ኤድስ ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38 ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ለ37ኛ ጊዜ በተለያዩ ሁነቶች ታስቦ ውሏል።

.