የሲዳማ ክልል ልዑክ በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ማካሄድ ጀመረ።
ጥር 14/2018 ዓ.ም
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የሥራና ክህሎት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች የተመራ ልዑክ በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ማካሄድ ጀምሯል።
የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ መድረኩ የእንኳን በደህና መጣችሁ አቀባበል በማድረግ የተጀመረ ሲሆን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንደገለፁት ልዑኩ የመጣበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ24/7 አዲስ የስራ ባህል ተፈጥሮ አስደናቂ ውጤት እያመጣ በሚገኝበት ጊዜ መሆኑ ለልምድ ልውውጡ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
አቶ ሚሊዮን በተጨማሪም በቢሮው እየተተገበረ ያለው በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ የዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ስራ ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የሲዳማ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊና የልዑኩ መሪ አቶ ከፍያለው ከበደ በበኩላቸው የልዑክ ቡድኑ አባላት በቆይታቸው በተቋም ግንባታ፣ በፍትሀዊ ተጠቃሚነት፣ በተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር፣ በተገኙ ውጤቶችና በራስ አቅም የበለፀጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዙሪያ ሰፊ የልምድ ልውውጥ እንደሚያካሄዱ ገልፀዋል።
የልምድና ተሞክሮ ልውውጡ ከመድረክ ውይይት በኋላ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች እና በተመረጡ ክፍለ ከተሞች የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

.